፩ አቤቱ ንጉስ ሆይ እገዛልሃለሁ፤ አቤቱ! አምላኬና መድኀኒቴ አመሰግንሃለሁ፤ በስምህም እታመናለሁ፤
፪ ረድተኸኛልና ሰውረኸኝማልና፤ ሰውነቴንም ከሞት አድነኸዋልና፥ ከአንደበት የነገር ሥራ ወጥመድም አድነኸኛልና፥ ሐሰትንም ከሚሰሩአት ከብዙ ሰዎች ምላስ አድነኸኛልና፥ በጠላትነትም ከተነሱብኝ ሰዎች ፊት የምትረዳኝና የምትሰውረኝ ሆነሃልና።
፫ እንደ ቸርነትህ ብዛት መጠን ስለ ስምህ አዳንኸኝ። ይበሉ ዘንድ ያዘጋጁትን እንደሚያመሰኩ እንደዚሁ ባገኘችኝ በመከራዬ ብዛት ሰውነቴን ፈለጓት።
፬ ቋያ እንደ ከበበው፥ በእሳት መካከልም እንደማይቃጠል፥
፭ ከታችም ከመቃብር ሆድ፥ ከረከሰ አንደበትም፥ ከሐሰት ቃልም አዳንኸኝ፤
፮ ወደ ንጉስ በሚያጣላ ዐመፀኛ አንደበት፥ ሰውነቴ ወደ ሞት ደረሰች፤ ሕይወቴም ወደ መቃብር ደረሰች።
፯ በዙሪያዬም ከበቡኝ፤ የሚረዳኝም አጣሁ፤ የሚያድነኝ ሰው እንዳለ ብዬ ተመለከትሁ፤ ግን ማንም አልነበረም።
፰ አቤቱ ይቅርታህን ዐሰብሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የነበረ ሥራህን ዐሰብሁ አንተን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች፥ ከጠላታቸውም የምታድናቸው ብፁዓን ናቸውና።
፱ ልመናዬንም ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ አደረግሁ፤ ከሞት እድን ዘንድ ጸለይሁ።
፲ አባቴና ጌታዬ እግዚአብሔርንም ረዳት በሌለበት፥ ትዕቢተኞች በተነሱበት ወራት በመከራዬ ጊዜ አትለየኝ አልሁት።
፲፩ ስምህንም ለዘለዓም አመሰግናለሁ፤ እገዛልሃለሁ፤ ምስጋናህንም እናገራለሁ፤ ልመናዬን ሰማኸኝ።
፲፪ ከሞትም አዳንኸኝ፤ መከራ ከሚመጣበት ቀንም አዳንኸኝ፥ ስለዚህም ነገር እገዛልሃለሁ፥ አመሰግንሃለሁም። አቤቱ ስምህን አመሰግናለሁ።
፲፫ እኔ ሕፃን ሳለሁ ሳልሳሳት ጥበብን መረመርኋት፤ በጸሎቴም መረጥኋት።
፲፬ በቤተ መቅደስም ስለ እርስዋ ለመንሁ፤ ለዘለዓለምም እመረምራታለሁ።
፲፭ ፍሬዋም እንደ ተክል ፍሬ በዛ ፤ ልቦናዬም በእርስዋ ደስ አለው፤ እግሬም በእውነት ቆመች፤ ከሕፃንነቴም ጀምሮ ፍለጋዋን ተከተልሁ።
፲፮ በጆሮዬም ፈጽሜ አደመጥኋት፤ መረጥኋትም፤ እኔም ብዙ ጥበብን አገኘሁ።
፲፯ በእርሷም ከፍ ከፍ አልሁ፤ ጥበብን የሰጠኝን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።
፲፰ አደርጋትም ዘንድ ዐሰብሁ፤ ለበጎ ነገርም ቀናሁ፤ አላፍርምም።
፲፱ ሰውነቴም በእርስዋ ተበረታታች፤ በሥራዬም ተራቀቅሁ፤ እጆቼንም ወደ ላይ አነሣሁ፤ ለድንቁርናዬም አለቀስሁላት።
፳ ሰውነቴንም ወደ እርስዋ አቀናሁ፤ በንጽሕናም አገኘኋት፤ ልቡናዬንም ከመጀመሪያ ጀምሮ ከእርስዋ ጋር አጸናሁ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አልጣለኝም።
፳፩ ሰውነቴም ለእርስዋ ታወከች፤ መረመረቻትም፤ ስለዚህም መልካም ሀብትን ገንዘብ አደረግሁ።
፳፪ እግዚአብሔርም አንደበትን ዋጋ አድርጎ ሰጠኝ፤ በእርስዋም አመሰግነዋለሁ።
፳፫ እናንት አላዋቂዎች ወደ እኔ ቅረቡ፤ በጥበብ ቤትም ትኖራላችሁ።
፳፬ እንዴት አጣችኋት? እስኪ ንገሩኝ! ሰውነታችሁስ ፈጽማ እንደ ምን ተጠማች?
፳፭ አፌን ከፍቼ "ያለ ዋጋ ገንዘብ አድርጓት" ብዬ ተናገርሁ፤
፳፮ አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ቀንበሯንም ተሸከሙ፤ ሰውነታችሁም ጥበብን ትቀበል፤ እርስዋን ማግኘት ቅርብ ነውና።
፳፯ እነሆ ጥቂት ደክሜ በእርስዋ ብዙ ዕረፍትን እንዳገኘሁ፤ በዐይናችሁ ተመልከቱ።
፳፰ ከብዙ ብር ይልቅ ጥበብን ምረጧት፤ ቊጥር ከሌለው ከወርቅ ይልቅ ገንዘብ አድርጓት።
፳፱ ሰውነታችሁም በቸርነቱ ደስ ይበላት፤ እርሱንም ማመስገን አትፈሩ።
፴ በጊዜው ዋጋችሁን ይሰጣችሁ ዘንድ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሥራችሁን ሥሩ። የሲራክ ጥበብ ተፈጸመ።